📖 የዮሐንስ ራእይ 8
-
1
¶ ሰባተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ እኵል ሰዓት የሚያህል ዝምታ በሰማይ ሆነ።
-
2
በእግዚአብሔርም ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ፥ ሰባትም መለከት ተሰጣቸው።
-
3
ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሰዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሰዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው።
-
4
የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ።
-
5
መልአኩም ጥናውን ይዞ የመሰዊያውን እሳት ሞላበት ወደ ምድርም ጣለው፤ ነጐድጓድና ድምፅም መብረቅም መናወጥም ሆነ።
-
6
ሰባቱንም መለከት የያዙ ሰባቱ መላእክት ሊነፉ ተዘጋጁ።
-
7
ፊተኛውም መልአክ ነፋ፤ ደምም የተቀላቀለበት በረዶና እሳት ሆነ፥ ወደ ምድርም ተጣለ፤ የምድርም ሲሶው ተቃጠለ የዛፎችም ሲሶው ተቃጠለ የለመለመም ሣር ሁሉ ተቃጠለ።
-
8
ሁለተኛውም መልአክ ነፋ፤ በእሳት የሚቃጠል ታላቅ ተራራን የሚመስል ነገር በባሕር ተጣለ፤ የባሕርም ሲሶው ደም ሆነ
-
9
በባሕርም ከሚኖሩ ሕይወት ካላቸው ፍጥረቶች ሲሶው ሞተ የመርከቦችም ሲሶው ጠፋ።
-
10
ሦስተኛውም መልአክ ነፋ፤ እንደ ችቦም የሚቃጠል ታላቅ ኮከብ ከሰማይ ወደቀ፥ በወንዞችና በውኃም ምንጮች ሲሶ ላይ ወደቀ። የኮከቡም ስም እሬቶ ይባላል።
-
11
የውኃውም ሲሶ መራራ ሆነ መራራም ስለተደረገ በውኃው ጠንቅ ብዙ ሰዎች ሞቱ።
-
12
አራተኛውም መልአክ ነፋ፤ የፀሐይ ሲሶና የጨረቃ ሲሶ የከዋክብትም ሲሶ ተመታ፥ የእነዚህ ሲሶ ይጨልም ዘንድ፥ የቀንም ሲሶው እንዳያበራ፥ እንዲሁም የሌሊት።
-
13
አየሁም፥ አንድም ንስር በሰማይ መካከል እየበረረ በታላቅ ድምፅ። ሊነፉ ያላቸው የሦስቱ መላእክት መለከት ስለሚቀረው ድምፅ በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው፥ ወዮላቸው፥ ወዮላቸው ሲል ሰማሁ።